ላለፉት በርካታ ሳምንታት ለሰላማዊ መፍትሄ ዕድል ለመስጠት በማሰብ ከዓፋርና ከአማራ ክልል ሰራዊታችን ለማስወጣት መወሰናችን ይታወቃል። ይሁንና በፌደራል መንግስት በኩል ሰራዊቱ ከትግራይ ድንበር ባሻገር ባለበት እንዲቆም ወስኛለሁ ቢልም በትግራይ ሰራዊት ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ሲፈፅም ቆይተዋል።

በተለያዩ ይዞታዎቻችን ላይ የተደረጉትን ትነኮሳዎች በመቛቋም እንዲሁም አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ የእርምት እርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር የኣለምኣቀፍ ማህበረሰብን የሰላም ጥረት እድል ለመስጠት በማሰብ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎቹን በትዕግስት ለማለፍ ስንሞክር ቆይተናል። ከዚሁ በተጫማሪ ህዝባችን ላይ የተጣለውን ሰው ሰራሽ ረሃብ ለማቃለል ያግዛሉ ያልናቸውን እርምጃዎችን ስንወስድ ቆይተናል።

በትግራይ መንግስት በኩል እነ አወል ዓርባ የዓፋርና የትግራይ ህዝቦች ያላቸውን ታሪካዊ ትስስር ለማዳከምና የተሰጣቸውን እኩይ አጀንዳ ለማስፈፀም በትግራይ ይዞታዎች ላይ የፈፀሟቸውን ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን: እንዲሁም አለምአቀፍ ማሕበረሰብ የሚያደርጋችው የሰብኣዊ አርዳታ የማቅረብ እንቅስቃሴዎችን በተደራጀ መልኩ የማደናቀፍ እኩይ ስራ እንዲያቆሙ በዓፋር የሃገር ሽማግሌዎች በኩል ለማግባባት ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይሁንና በራሳቸው ሚድያ ስለ ትግራይ ሰራዊት መዳከም በተደጋጋሚ የሚያወሩትን ውሸት በማመንና በተለይም በኤርትራ መንግስት የሚሰጣቸው ቀጥተኛ ድጋፍ በመበረታታት የትግራይ ድንበርን በመጣስ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀሙን ቀጥሏል::

ከዚህ ጠብ ኣጫሪ መንፈስ በመነሳት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የእርዳታ ማድረስ እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል በማቀድና የትግራይ ዋና ከተማ መቐለንና የአከባቢውን ደህንነት ለማወክ በኤርትራ መንግስት ቀጥተኛ አመራር የቀይ ባሕር አፋር ሃይል በሚል ሽፋን የተደራጀ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ሃይሎችን ጭምር በማሰማራት የአወል ዓርባ ልዩ ሃይሎች የጀመሩትን ጥቃት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሱበት ሁኔታተፈጥሯል::

ይህ አደገኛ ጠብ ኣጫሪ እርምጃ ከትላንትና ወዲያ ጧት ጀምሮ ከመቐለ በስተምስራቅ እስከ ራያ ጫፍ ባሉ ይዞታዎች ላይ በተቀናጀ መልኩ ትንኮሳዉን በማጠናከር የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እህል የማቅረብ እንቅስቃሴ ለመስተጓጎልና የመቐለን ከተማ ፀጥታ በከፍተኛ አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ በዓይነቱ ለየት ያለ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

የትግራይ ሰራዊት ከነሙሉ ዓቅሙ እያለ፣ ለሰላም ዕድል ለመስጠትና ከሁሉም በላይ ግን በዓፋርና በትግራይ ህዝቦች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር ያሰቡ ፀረ ህዝቦች ባዘጋጁት ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት፣ ከመቐለ ከተማ ከ30 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት የተከፈተብንን ጥቃት ከመከላከል በዘለለ ግጭት አባባሽ እርምጃዎችን ሳንወስድ ከስድስት ሳምንታት በላይ ታግሰናል። ሆኖም በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም::

በዚህም መሰረት በሃገር ሽማግሌዎች የተደረጉ ጥረቶችን፣ የትግራይ መንግስት ተደጋጋሚ ይፋዊ የሰላም ጥሪዎችን ከቁብ ባላመቁጥር የትንኮሳ ጥቃት ሲያካሂድ በነበረው የአወል ዓርባ ልዩ ሃይልና የኤርትራ መንግስት ያደረጃው የቀይባሕር ዓፋር ሃይል ተብሎ የሚጠራ ቡዱን ላይ ከትናንተና እለት ጀምሮ እነዚህ ሃይሎች ቀጣይ ሰጋት የማይሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገደናል::

የተወሰደው እርምጃ ኣላማ በዋናነት የአወል ዓርባ ጠባጫሪ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ተላላኪዎችን ከጥቅም ውጪ በማድረግ ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት እንቅፋት ሆነው መቀጠል ወደማይችሉበት ደረጃ ለማውረድ ነው:: የተከተልነው ወታደራዊ ስልትም በመሰረቱ አቅማቸውን ከማዳከምና: ይዘዋቸው ከነበሩ የትግራይ የዞታዎችና ለትግራይ ቅርብ ከሆኑ ማስፈንጠርያ ቦታዎች ከመጠራረግ በዘለለ ደም ኣፍሳሽ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ የተከተልን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳልን::

እስካሁን በተወሰደው እርምጃ በርካታ የአወል ዓርባ ልዩ ሃይል ኣባላትን ጨምሮ የኤርትራ መንግስት ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ውለዋል:: ከዚህም በተጨማሪ በእስር የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን የትግራይና የዓፋር ተወላጆችን ነፃ ለማውጣት ችለናል:: የትግራይ መንግስት ሰራዊቱን በዓፋር ክልል ይዞታ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የማቆየትም ሆነ የተጀመረውን ግጭት ወደ ተባባሰ ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት እንደሌለውና የቆየውን የሁለቱ ሀዝቦች መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል ይልቁንም እንዲጠናከር ያለውን ዝግጁነት ይገልፃል::

የትግራይ ህዝብና መንግስት የዓፋር ህዝብ ወንድሙ ከሆነው የትግራይ ህዝብ ጋር ሊያጋጩት ሌተ ቀን የሚሸርቡትን ፋሽስት መሪዎቹን አደብ ሊያስገዛቸው እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ ይወዳሉ:: በዚህ ኣጋጣሚ አለም አቀፍ ማህበረሰብ የትግራይ ሰብኣዊ ሁኔታ በሚመጥን መልኩ የሰብኣዊ እርዳታ ክልከላው ባስቸኳይ እንዲነሳ ጥረቱ እንዲያጠናክር እየጠየቅን የትግራይ መንግስት በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጅነቱን ይገልፃል::

የዓፋርና የትግራይ ህዝቦች ታሪካዊ ግንኙነት አይበጠስም!
መቐለ

metkel mediahttp://www.metkelmedia.com

Share.

Leave A Reply